መነበብ ያለባቸው

የካሊድ መንገድ – በሁዳ ኬ

ከካሊድ ጋር የተዋወቅነው ትምህርት ቤት ነው፡፡ ፈታ ያለ ልጅ ነው፡፡ ምንም ነገር ለማድረግ ከቤተሰቡም ሆነ ከሌሎች ሰዎች አይደባበቅም፡፡ ይቅማል፣ ያጨሳል- ማለቴ ሺሻም ይሞክራል፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔና ሌሎች በቡድን የምናስብና የምንንቀሳቀስ የካሊድ ጓደኞች ጫትም ሆነ ሺሻ የለመድነው እሱን ታከን ነው ብል ለእውነት ሩብ ጉዳይ ሀቅ እንዳወራሁ ነው የሚሰማኝ፡፡

ምላሱ ላይ የተነቃሳት የምትመስለን የካሊድ እናት የሁላችንም እናት እንደዛ በሆኑልን ብለን እስክንመኝ ትመቸናለች፡፡ ባጠቃላይ የካሊድ አኗኗር ህልማችን ነው፡፡ እርግጥ ነው ከሱ ጋር በነበረን ትስስር ከዲናችን እየራቅን መምጣታችን ሳይታወቀን ነጉደን ነበር፡፡ እስማኤል እስኪቀላቀለን፡፡ ባጭሩ እስማኤል ሙሴያችን ሆኖ ታደገንና የተበላሸው ሂወታችን መስመር እየያዘ ወደ አላህ እየተቃረብን በኢባዳ እየበረታን‹ ከሱስ እየተፋታን መጣን፡፡

የዚህን ጊዜ በካሊድና በእናቱ መሃከል ያለው ክፍተት በደንብ ገባን፡፡ ካሊድ በዙርያው ጓደኛ እንጂ ቤተሰብ እንደሌለው ተረዳን፡፡ እንዴት ማለት ጥሩ… እንዴት በሉ… የካሊድ እናት ካሊድን ስትወልድ ልጅ ወልዶ ለማሰደግም ሆነ ከስሜት ከፍ ብሎ ስለማሰብ ደንታ አልነበራትም፡፡

ይህን ስል አዝናለሁ ነገር ግን የሆነው እንደዛ ነው… አለማወቅ ሊሆንምኮ ይችላል፡፡ ቢሆንም ካሊድ ከልጅነቱ ጀምሮ ያደገው ፐ! ዘመናዊ እናትስ እንደሱ እየተባለ በሌሎች እየተቀናበት ቢሆንም… በዘመናዊነት ስር የተደበቀው የናቱን የናትነት ሚና መጉደል ማንም ሳያስተውልለት ክፍተቱን እያሰፋ ነው ያደገው፡፡ እናቱ ከልጇ ፊት ልትደብቀው ያልቻለችው አላህን የሚያስቆጣ ባህሪና ተግባራቶቿ በሱ የልጅነት ሚዛን ልክ ናቸው ተብለው ሲሰፈሩ ነው ያደገው፡፡

ወላጆቹ ጥፋታቸውን፣ የወላጅነት ሚናቸውን ባለመወጣታቸው ምክንያት የሚመጣውን ቀውስ ለልጃቸው የፈለገውን ነገር እንዲያደርግ በመፍቀድ ነው ያካካሱት፡፡ በህይወቱ ክልከላ የለም፡፡ ህግ የለም፡፡ ስርዓት የለም፡፡ ማድረግ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደሚችል ነው የሚያውቀው፡፡ መቃም የፈለገ ቀን እናቱ ጋር ፈርሾ፣ መውጣት የፈለገ ቀን ሴት ጓደኞቹን በናቱ ስልክ ጠርቶ ማማዬ ዛሬ አድራለሁ አትጠብቂኝ ብሎ ራስህን ጠብቅ ተብሎ ነው የኖረው፡፡ ከሙስሊም ቤተሰብ ቢወለድም የእስልምና ድንበር የት ድረስ እንደሆነ ሳይነገረው፣ ከዚህች ሀገር ተሸግሮ ሌላ ህይወት እንደሚጠብቀው ሳያውቅ ነው የኖረው፡፡

ከኛ ጋር የገጠመ ሰሞን ለሰላት የምናሳየው መጠዳደፍ ይገርመው ነበር፡፡ በዚህ እድሜያችን ለመስገድ ማሰባችን ራሱ ይደንቀዋል፡፡ ለሱ የሚገባው ሰላት የትልልቅ ሰዎች ጉዳይ እንደሆነ ነው፡፡ ዲን ማለት ለሱ ቤታቸው ተፈርሾ ዱኣ ሲደረግ አሚን፣ አሚን በሚባለው ኢባዳ የተወሰነ ነው፡፡ ሙስሊም መሆኑን ቢያውቅም እስልምና እንደብሄሩ ወይም ጾታው የተጫነበት አንድ ማንነት እንጂ ህግና ስርዓት ያለው የህይወት መመርያ መሆኑን አያውቅም፡፡

ቁርዓን መቅራት ቢችልም ወደ አላህ በመከጀል ሚቃረቡበት መሳርያ መሆኑን አይገነዘብም፡፡ ባጠቃላይ ለሱ አለም እናቱ ባሰመረችለት መስመር ውስጥ የሚርመሰመስ ዑደት እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡

ያው እንዳልኳችሁ እስማኤል ህይወታችንን እስኪቀላቀል ድረስ በካሊድ መንገድ የምንጓዝ ስድስት ዘባተሎ ጎረምሶች ነበርን፡፡ አሁን አልሀምዱሊላህ በእስማኤል መንገድ ሄደን አላህን ለማግኘት የምንተጋ አራት ወጣቶች ሆነናል፡፡ አስተዳደጉን ሳውቅ አላህ በቁድራው አንዳንድ ሰውን ይጠብቃል እላለሁ፡፡ በልጅነታችን መድረሳ አድገን በየፊናችን የተበታተንን የዲን እውቀት እስኪበቃን የጠጣን የመስጅድ ልጆች የተዘፈቅንበት ወንጀልና አላህ አንዳንድ ባርያዎቹን ወደሚፈልገው መንገድ የሚመራበት የራሱ ጥበብ አለው ያስብለኛል፡፡ የካሊድ መንገድ ያሰመጣቸው ሁለት ጓደኞቼን ሁኔታ የምገነዘበውም በዚሁ መልኩ ነው፡፡

የመልካም ሙስሊምነትን ጎዳና ከያዝን በኃላ የጎደሉትን ባልንጀሮቻችንን ወደዚህኛው መንገድ ልንመልሳቸው ቀን ከሌት ብንለፋም አልተሳካልንም፡፡ አንድ ሰው ተባብሮ አምስታችንንም ሲያፈርሰን ባይከብደውም፣ አምስት ሆነን ሁለት የወጣት ነብሶችንን መገንባት ግን ከብዶናል፡፡ ከሁላችንም በላይ በጠፉት በጎች ላይ ሃላፊነት ተሰምቶት የለፋው ካሊድ ቢሆንም እንደቀደመው ቀላል አልሆነለትም፡፡

የካሊድ የዛሬ ህልም አዲስ ተጋቢዎች ከሰርጋቸው በፊት ስለልጅ አስተዳደግ ትምህርት የሚሰጥ ማዕከል መገንባት ነው፡፡ ምክንያቱም የእሱ እናት ያንን ባለማወቋ ከሱ ውስጥ ያጎደለችውን የሚያውቀው እሱ ነውና፡፡

ይህ ታሪክ ሙስሊም ወጣቶች ከዲናቸው እንዲርቁ ከሚያደርጋቸው እጅግ ብዙ ምክንያቶቹ አንዱን ነው የሚያሳየን፣ ነገር ግን በተመሳሳይ አብዛኞቹ የስነምግባር ችግሮችና ውጥንቅጦች ዋናው መንስኤ ወላጆች በልጆቸቸው አስተዳደግ ወቅት በሚፈጽሟቸው ስህተቶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ልጅ ወልዶ ማሳደግ ቀላል ሃላፊነት አይደለም፡፡ ብዙዎቻችን ጎጆ በመመስረት ሂደት ውስጥ ግን ስለልጆቸ አስተዳደግና ስለሚኖርብን ሃላፊነት የምናስብ አይመስለኝም፡፡ አንዲት ሴት ለአራት ነገሮች ትገባለች ለመልክ፣ ለሀብት፣ ለዘርና ለዲን… ዲን ያላትን አግቡ ሲሉን ውዱ ሰው ነብዩ መሀመድ (ሰ.ዓ.ወ.) ዲን ያላት ሴት ቤቱን በማቆም ሂደት ውስጥ ያላትን ሚና ስለሚገነዘቡ ነው፡፡ ቤት በምንለው ማዕቀፍ ውስጥ ደሞ በዋነኝነት በተለይ እንደዚህ ውጥንቅጡ በጠፋበት አለም ውስጥ ልጆች ዋነኞቹ የትኩረት ማዕከል መሆነቸው የማይታበል ሀቅ ነው፡፡

ከዚህ በላይ የፃፍኩት ታሪክ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሰማኃቸው፣ ያስተዋልኳቸውና የታዘብኳቸው እውነቶች ተገጣጥመው ነው፡፡ እዚህ ያመጣሁት ልጆችን በማሳደግ ሂደት ውስጥ የሚሰጠን አንዳች ትምህርት ይኖራል በሚል ግምት ነው፡፡ ለመማር ዝግጁ ለሆነ ሰውአላህ በአጋጣሚዎች ሁሉ ሊያስተምረን እንደሚፈልግ እንድናውቅለት ይመስለኛል በተደጋጋሚ አስተንትኑ የሚለን፡፡

የበለጠውንንና የተሻለውን እርሱ ያውቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button

People Who viewed ThisX

የማስታወቂያ ማገጃ አብርተዋል!

ድረ ገፁን ለመጎብኘት እባክዎን በመጀመርያ የማስታወቂያ ማገጃዎን ያጥፉ።